ህይወታችንን የሚቀይረው፣ እርምጃችንን የሚያስተካክለው፣ መንገዳችንን የሚያሳልጠው፣ ወደፊት የሚመራን፣ የስኬት ሚስጥር የሚሆነው ሁነኛው አጋጣሚ ከአዕምሮ ይመነጫል፤ ከፍላጎት ይነሳል፤ ከስሜት ይቀዳል።
ቀላል ስለሆነ ሳይሆን ምርጫችን ስለሆነ ብቻ ፍሬን ያፈራል።
የማይመረዝ ስለሆነ ብቻ ለተሻለ ስፍራ ያበቃናል
የኛ በመሆኑ ብቁ ያደርገናል
ከውስጥ በመውጣቱ ክፍታውን ያስጨብጠናል
ከመንፈስ በመገናኘቱ ሃይልና ብርታ ይሆነናል።
ህይወትን የሚቀየረው ከሶስተኛ ወገን በሚመጣ ሃሳብ ከውጪ በምናየው እንቅስቃሴ ወይንም በሚነገረን አፈታሪክ ሳይሆን ከእኛ በሚነሳው ሁሌም በሙላት በሚፈሰው ገደብ አልባ ፍላጎትና የልብ መሻት ነው።
አዕምሮ ማውጣት ማውረድ እስካላቆመ ድረስ ማሰብ ማሰላሰል አማራጭ መንገዶችን መፈለግ ህልምን ማሰስ አጋጣሚዎችን መፍጠር እስካላቆመ ድረስ ከአይነተኛው አስገራሚ ለውጥ የሚያቆመንና የሚያስተጓጉለን አንድም አካል የለም።
ከፈጣሪ የተቸረን ስጦታ በመንፈሳዊው ሀይል በአዕምሮ መስኮት በኩል ይመነጫል ከማንነታችን ይነሳል።
ለየትኛውም እድገት ምንጩ እኛ ነን።
መነሻው አዕምሯችን ነው መሰረቱ የውስጣችን መንፈሳዊነት ነው። የማንም እጅ መጠበቅ፣ በማንም ተረጂ መሆን፣ ዘወትር አድናቂና አወዳሽ ብቻ መሆን፣ በተረት ተረት ራስን ማታለል፣ የሌላው አወዳሽና አሞጋሽ መሆን እስከተወሰነ ጊዜ ሊያዋጣን ይችል ይሆናል። ነገር ግን አንድ እስከ መቼ የሚል ጥያቄን አስከትሎ ይመጣል።
አቅም ስላጣን፣ ክህሎት ስላነሰን፣ ብርታቱን ስለተነፈግን፣ ስንፍና ስለተቆጣጠረን ሳይሆን ስለፈለግን ብቻ የዚህ ህይወት ገፈት ቀማሽ እንደሆንን መገንዘብ ይኖርብናል።
“የሚረዱኝ ባይኖሩ፣ከራሴ ውጪ ምርጫ ባይኖረኝ፣ትክክለኛውን የውስጥ አቅሜን ብረዳ በእርግጥ በዚህ አሰልቺና አስኮናኝ የህይወት ፈርጅ ውስጥ እገኝ ይሆን?” ብለን እራሳችንን እንጠይቅ።
በእርግጠኝነት ይህን በመሰለ አዙሪት ውስጥ እንደማንገኝም እናውቀዋለን።
አማራጮች ሲበዙ፣ምቾት ሲቆጣጠረን፣አውቅልሃለው ባዮችን ስንሰማ፣አቅማችንን ሳንረዳ ስንቀር በራሳችን መቆም ይሳነናል፤አዕምሯችንን ማሰራት፣የፈጠራ አቅሙን ማጎልበት፣ለራስ የሚሆን መገለጫ ማበጀት እንዳይችል እናደርገዋለን።
በነፃ ሃሳብ፣በሰከነ አዕምሮ፣በብሩህ እይታ ውስጥ ሁሌም እጅግ አስደናቂና አስገራሚ የህይወት አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ።
አንድና አንድ የሚጠይቁት ነገርም ያለማቋረጥ ወደ ውስጥ መመልከት፣የልብ ትርታን ማዳመጥ፣የህይወት ጥሪን መለየት ነው።
በምንም ተዓምር የማናቆመው፣ነፍስን የምናስገዛለት፣እራሳችንን የምናንፅበት ነገር ይህ የህይወት ዘመን ጥሪ ነው።
ውስጣችን ያለው ምንጭ ከአምላክ መንፈስ ጋር የተገናኘ፣ እኛን ብቻ የመረጠ፣በእኛ ላይ ብቻ ያደረ እፁብ ድንቅ ስጦታችን “አዕምሯችን” ነው።
ውስጣችንን ለመመልከት ጊዜ አናጥፋ፣ራስን ለማዳመጥ አንስነፍ፣አዕምሮን ለማሰራት አንታክት፣አቅምን ለማውጣት አንሰላች፣የእኛ የሆነውን መለያ ለመፍጠር በፍፁም ተስፋ አንቁረጥ።
በምክንያት የተሰጠን፣ተመርጦ የተለገሰን ግሩም ስጦታ አዕምሮ ባለበት ራስን በተረጂነትና በስንፍና አንገድበው።
እግዚአብሔር ማስተዋልን፣ጥበብን፣እውቀትን ከፍቅር ጋር ይስጠን።
አሜን🙏